የኢትዮ-ቴሌኮም ሽያጭ ጉዳይ፤ ሰሚ ያጣ ጩኸት!

    የኢትዮ-ቴሌኮም ሽያጭ ጉዳይ፤  ሰሚ ያጣ ጩኸት! 

(ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ) – ሲራራ – Sirara

የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ ለሁለት የውጭ ተቋማት በኢትዮጵያ ቴሌኮም ዘርፍ ላይ እንዲሳተፉ የጨረታ ፈቃድ መስጠቱ ተሰምቷል፡፡ ይህም መንግሥት ቴሌኮም ዘርፉን ወደ ግል ለማዛወረው ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት መሆኑን ያመለክታል፡፡ ኢትዮ-ቴሌኮም መሸጥ እንደሌለበት በተደጋጋሚ በርካታ ባለሙያዎች ስንጮህ ብንቆይም ሰሚ ያገኘን አይመስለኝም፡፡ በበኩሌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጠሩት ስብሰባ ላይ ጭምር ኢትዮ ቴሌኮም መሸጥ እንደሌለበት አስረግጬ ብናገርም የተሰጠው ምላሽ ግን “እኛ ለመሸጥ ወስነናል” የሚል ነበር፡፡

ከዚህ ቀደም በተለያዩ መድረኮች ለማስገንዘብ እንደሞከርኩት፣ በቴሌ ሽያጭ በቀዳሚነት መነሳት ባለባቸው ጥያቄች፣ ማለትም ተቋሙ በዓለም ዐቀፍ ውድድር ውስጥ ገብቶ የመወዳደር አቅም አለ ወይ? ውድድሩን ተቋቁሞ መሥራትስ ይችላል ወይ? በሚሉት ጉዳዮች ላይ ትልቅ ስጋት አለኝ እንጂ ሌሎች ድርጅቶች ገብተው ቢወዳደሩ ችግር የለብኝም፡፡ በቴሌ ደካም አገልግሎት ከሚቸገሩት አንዱ ነኝ፡፡ እግዚአብሔር ይስጣትና ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ በቅርቡ ያደረገችው ከፍተኛ መሻሻል እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡

ሌላው ተቋሙን እንዲቆጣጠር ያቋቋሙት የኮምኒኬሽን ባለሥልጣን የመቆጣጠር አቅም ምን ያህል ጠንካራ ነው? የሚል በአግባቡ ትኩረት ተሰጥቶት መታየት አለበት፡፡ ባለሥልጣኑ በአዋጅ እንዲቋቋም ፈቃድ ካገኘ በትንሹ የአምስት ዓመት ልምድ እንኳን የለውም፡፡ እንድ ተቋጣጣሪ ተቋም ቢያንስ ከ10 ዓመት በላይ ልምድ ያላቸው ሰዎች የተሰባሰቡት ተቋም ሊሆን ይገባዋል፡፡ አዲሱ ተቋጣጣሪ ባለሥልጣን ባልዳበረ ልምድ እና ዕውቀት የዓለምን የቴሌኮም ዘርፍ የሚዘውሩ ተቋማትን ለመቆጣጠር መነሳቱ አስገራሚነትን የሚያጭር ነው፡፡




በቅርቡ ይህ ባለሥልጣኑ ባወጣው ሰነድ/አዋጅ አንድ አንቀጽ ላይ አሁን ያሉት የኢትዮ-ቴሌኮም ደንበኞች ከነ ሞባይል ቁጥራቸው አዲስ ወደሚገቡት ተቋማት መሄድ ይችላሉ ይላል፡፡ ይህን ስናይ ይህ ተቋም ተቆጣጣሪ ተቋም ቢሆንም የአገርን ጥቅም ማስከበር ሲገባው ገና ካፈጣጠሩ መሰል መመሪያዎችን ሲያወጣ እየተመለከትን ነው፡፡ እንዴት ልንተማመንበት እንደምችል ይከብዳል፡፡ በግሌ በዚህ ተቋም ላይ ያለኝ እምነት ደካማ ነው፡፡

በማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃ ብንመለከተው ተቋማቱ ከገቡ በኋላ ለሚሰጡት አገልግሎት ገንዘብ የሚሰበስቡት በብር ነው፡፡ ሲወጡ ግን ትርፋቸውን የሚፈልጉት በዶላር ነው፡፡ ዛሬ 3 ወይም 4 ቢሊዮን ብር ከሽያጩ ለማግኘት የምንወስነው ውሳኔ ነገ ተቋማቱ ትርፋቸውን በዶላር ሲጠይቁን ወደ ባሰ ችግር ውስጥ ነው የሚከቱን፡፡ ይኼ እንግዲህ አሁን ያለው ቴሌ ውድድሩን የመቋቋሙ ስጋት እንደተጠበቀ ሆኖ ነው።

በመንግሥት ስር ያሉ ተቋማት ወደ ግል መዛወሩ ላይ ተቃውሞ ባይኖረኝም ተቋማቱ ሲዘዋወሩ ግን አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ ማሟላት ይገባቸዋል፡፡ ተቋማቱ ወደ ግል ሲዘዋወሩ የሚዘዋወሩበት ምክንያትም በግልጽ መቀመጥ ይገባዋል፡፡

ኢትዮ-ቴሌኮም ሲሸጥ የአገልግሎት ቅልጥፍና ያመጣል የሚል መከራከሪያ ነው ሲቀርብ የምሰማው፡፡ በእኔ እምነት፣ በሲራራ ጋዜጣ ላይም ሆነ በሌሎች መድረኮች ደጋግሜ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲመጣ/እንዲኖር ወሳኙ ነገር ባለቤትነት ማዞር ሳይሆን የውድድር መድረክ መፍጠር ነው:: እነ ‹ኤም.ቲ ኤን› እና ቮዳፎንን የመሳሰሉ ተቋማት ገብተው ገበያው ላይ እንዲወዳደሩ መፍቀድ እንጂ ያለውን ተቋም ለነሱ መሸጥ በምንም ዓይነት መፍትሔ አይሆንም፡፡ መንግሥት ለዜጎቹ ቀልጣፋ የቴሌኮም አገልግሎት መስጠት ከፈለገ ማድረግ ያለበት የውድድር ሜዳውን ማስፋት እንጂ ያለውን አንድ ተቋም ለመሸጥ መሯሯጥ ተገቢ አይደለም።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንግሥት ድርጅት ሆኖም በዓለም ዐቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ መሆን ችሏል፤ አስቸኳይ የመንግሥት ዓይን የሚፈልገው የሠራተኞች፣ የሠራተኛ ማኅበሩና የአመራሩና ጽንፈኛ የብሄር ፖለቲከኞች ለግል ጥቅም በሚያደርጉት ጉዞ እንዳያፈርሱት የማደረግ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡ ተቋሙ ትርፋማ እና ተወዳዳሪ የሆነው ድርሻውን ለውጭ ድርጅቶች ሸጦ አይደለም፡፡ ጠንካራ አስተዳደር ስላለው ነው:: በቴሌኮምም ተመሳሳይ ነገር ቢፈጠር ትርፋማ የማይሆንበት ምክንያት አይታየኝም፡፡ በዓለም ላይ ጠንካራ የሆኑ የመንግሥት አትራፊ ድርጅቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ወደድንም ጠላንም የዚህች አገር የፈረንጅ ላም ነው፡፡ መንግሥት ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ በሚል ሲያልበው የኖረ ተቋም ነው፡፡ ይህን ተቋም በመሸጥ የምናጣቸው ሦስት መሠረታዊ ነገሮች አሉ፡፡

አንደኛ፣ ተቋሙ ባይሸጥ እንደ ዘንድሮ ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ ሲያገኝ ትርፉን ለተለያዩ ሥራዎች መጠቀም እንችላለን፡፡ ተቋሙ ከተሸጠ ግን ለውጭ ሀብታም ድርጅቶች ነው ትርፋችንን የምንሰጠው፤ ለዚያውም በዶላር ቀይረን፡፡ እሱም ዶላር ካለን ነው፡፡ ካልሆነ ‹ኤም.ቲ.ኤን› ናይጀርያ እንዳደረገው ሕገ-ወጥ ገበያ ገብቶ ዶላር ሲገዛ ገበያውን መረበሹ፣ ያሁኑን እጥረት ማባባሱ፣ በዚህም ግሽበት ማንገሡ አይቀሬ ነው፡፡ ካሁኑ ገደብ ያስፈልጋል።

ሁለተኛ፣ ኢትዮ ቴሌኮም ለውጭ ድርጅቶች የሚሸጥ ከሆነ አሁን በስልክ የምናወራው ወሬና ጠቅላላ የአገር ደህንነት አዳጋ ላይ ነው የሚወድቀው፡፡ ይህ ደግሞ ለውጭው የስለላ ዓለም በርን ወለል አድርጎ እንደመክፈት ነው የሚቆጠረው፡፡ ይህንንም በትግራይ ከነበረው የፌደራልና የክልሉ ልዩ ኀይል ከሚባለው ኀይል ጋር ከነበረው እሰቃቂ የሕግ ማስከበር ጦርነት ተምረናል ብዬ ተስፋ አደርጋለው።

ሦስተኛውና ብዙ ሰው ያላስተዋለው ነገር፣ አብዛኛው የኢትዮጵያ ፋይናንስ ተቋም የተመሠረተው በኢትዮ ቴሌኮም ህልውና ላይ ነው፡፡ የቴሌን ድርሻ ወደ ግል ስናዞር የፋይናንስ ተቋሞቻችንንም አብረን ወደ ግል እንዳዞርን ነው መታየት ያለበት፡፡

መንግሥት ግን ይህ የፋይናንስ ገበያ አሁን ለሚመጡት ኩባንያዎች እንዳይከፈትና፣ ቀደም ሲል ብዙ ሀብት ያፈሰስንበትን የቴሌ መሠረተ ልማትንም የሚመጡት ኩባንያዎች ከቴሌ ተከራይተው እንዲጠቀሙ በማስገደዱ በከፊልም ቢሆን ጩኸታችንን ሰምቷልና ልናመሰግነው ይገባል፡፡ ወደ ፊት ግን የፋይናንሱ ጉዳይ በአንክሮ ሊታሰብበት የሚገባ በጣም ስትራቴጂያካዊ ጉዳይ ነው፡፡ የፋይናንስ ደህንነት ችግርም ይዞ እንደማይመጣ እርግጠኞች መሆን አንችልምና።

የኢትዮጵያ መንግሥት ተቋሙን ለመሸጥ የፈለገበት መሠረታዊ ምክንያት የዓለም ዐቀፍ ድጋፍ ለማግኘት እና ከአሜሪካ፣ ከምዕራባውያን እና ከዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ድጋፍና ይሁንታ ማግኘቱን በማሰብ ነው፡፡ አሁን አገራችን ካለችበት የዲፕሎማሲ ጦርነት (በተለይም ከምዕራባዊያን ጋር)፣ የምንዛሪ ፍላጎት፣ የሕግ ማስከበሩ የፈጠረው ፈተና እና ግድቡን የመጠበቅ የዶላር ወጪ አንጻር የመንግሥትን ችግር እረዳለሁ፡፡ በዚህ ጭንቅም ውስጥ ቢሆን ግን የረዥም ጊዜ የአገር ጥቅምን እንዳንስት ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል፡፡

ቴሌ ዓላማው ድርሻውን ሸጦ አቅም መፍጠር ከሆነ ለአገር ውስጥ ባለሀብት መሸጥ ዶላር ከተፈለገም ለትውልደ ኢትዮጵያን መሸጥ ይቻላል፡፡ ያ ካልሆነ ደግሞ በዓመት ከሚያተርፈው ገንዘብ ላይ መልሶ ፈሰስ ያድርግና አቅሙን ያጎልብት፡፡ የቴክኖሎጂ አቅምን ማሳደግ ከሆነ ዓላማው በአጭር ጊዜ እይታ ከውጭ ክህሎት ያላቸውን ሰዎችን መግዛት ይችላል፡፡ በመካከለኛ ጊዜ ደግሞ እንደ ወይዘሪት ፍሬሕይውት ዓይነት ትንታግ አመራር ስላለ ሰው ማሰልጠን ነው። ወይም ኢትዮጵያውያኑን ልኮ የማሰልጠንና የማስተማር ዕድል አለው፡፡ መሸጥ እንደ ብቸኛ አማራጭ መታየት የለበትም፡፡ የቴሌን አቅም ለማሳደግ በጣም በርካታ አማራጮች አሉን፡፡ በእነሱ ላይ ነው ትኩረት ማድረግ ያለብን፡፡

አሁን ከሚመጡት አንዱ ‹ኤም.ቲ.ኤን› የተባለው ኩባንያ ከዚህ ቀደም ናይጄሪያ ገብቶ ሲም ካርድ ሳይመዘግብ ለቦኮሃራም ሳይቀር ሲሸጥ ቆይቶ 5 ቢሊዮን ዶላር አጭበርብሮ ሲያስወጣ ሁሉ የተያዘ ነበር፡፡ የናይጄሪያ መንግሥት ሊያባርረው ሲል በፕሬዚዳንት ራማፎዛ ምልጃ 1.5 ቢሊዮን ዶላር እንዲከፍል ተደረገ፡፡ የውጭ ተቋማት በገበያው ላይ ሲገቡ መሰል የደህንነት ስጋቶች አብረው እንደሚገቡ መታሰብ ይገባዋል፡፡ ለዚህም ቢያንስ የተቋጣጣሪ አቅም የሚጎለብትበትንና ሌላ የረቀቀ የመቆጣጠሪያ መንገድ መፈልግ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ይህ ሁሉ ታዲያ ተቋሙን ሸጠን ማጣፊያው ሳያጥረን ነው።

0/Post a Comment/Comments