“የአማራ ልሂቅ/ኢሊት”፣ የህወሃት፣ ርዕዮት ሚዲያ እና ትግራይ ሚዲያ ሃውስ አዲሱ የፀረ አማራ ዘር ፍጅት ቅስቀሳ መርዛማ ትርክት ማጠንጠኛ

 

“የአማራ ልሂቅ/ኢሊት”፣ የህወሃት፣ ርዕዮት ሚዲያ እና ትግራይ ሚዲያ ሃውስ አዲሱ የፀረ አማራ ዘር ፍጅት ቅስቀሳ መርዛማ ትርክት ማጠንጠኛ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህወሃት እና የህወሃት ልሳን ብዙሃን መገናኛወች አዲስ የፀረ አማራ ትርክት ቃል ይዘው መጥተዋል፣ “የአማራ ልሂቃን/ኢሊት” የምትል። ለመሆኑ ልሂቅ (በእንግሊዝኛው ኢሊት) ምን ማለት ነው? ልሂቅ ማለት በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ፦ በትምህርት፣ በዕውቀት፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በስፖርት፣ በስነጥበብ፣ በሃይማኖት እና መሰል ነገሮች በአንዱ ወይም ከአንድ በላይ በሆነ ልቀው የተገኙ ሰወች ማለት ነው፤ በአጭሩ ልሂቃን የአንድ ማህበረሰብ አስኳል ናቸው። በዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩ፣ የታመሙትን የሚያክሙ፣ሃገር የሚያስተዳድሩ፣ በፍርድ ቤት ተቀምጠው የሚዳኙ፣ በጥበብ ስራቸው ህዝብን የሚያዝናኑ፣ የሚያስተምሩ እና የሚያነቁ፣ ሃይማኖት የሚሰብኩ፣ በስፖርት ሃገር የሚያስጠሩ፣ ባለሃብት ሁነው ስራ የሚፈጥሩ ወዘተ ልሂቃን ተብለው ይጠራሉ። ስለዚህ የአማራ ልሂቃን ስንል ይሄን አስኳል የህብረተሰብ ክፍል ማለታችን ነው። 
 
የአማራ ልሂቃንን ሁሉ በአንድ ጨፍልቆ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለተፈጠረው ነገር ሁሉ ዋና ተጠያቂ ማድረግ የጀመረው የህወሃት ልሳን የሆነው ትግራይ ሚዲያ ሃውስ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የርዕዮት ሚዲያው ቴወድሮስ ፀጋየ ዋነኛ አስተጋቢው ሁኗል። ከቴወድሮስ ፀጋየ ጋር ርዕዮት ሚዲያ ላይ ብዙ ነገር አብረን ሰርተናል፣ በግልም ምንም አይነት ችግር የለብንም፣ ነገርግን ከጦርነቱ መነሳት በኋላ የሚሰራቸው ፕሮግራሞች ብዙወቹ የማልስማማባቸው እና የህወሃትን ፕሮፓጋንዳ ተቀጥላወች ናቸው። ለምሳሌ ቴወድሮስ ፀጋየ በፈረንጆቹ አፕሪል 1፣ 2021 በሰራው “ለባርነት ተሽቀዳድሞ ያልተመረጠው የአማራ ልሂቅ” [https://www.youtube.com/watch?v=d1bEid42aP4] የተሰኘ ፕሮግራም እንደዚህ ይላል “ የአማራ ልሂቅ ማለት ከሞላ ጎደል በአሁኑ ወቅት የአማራ ህዝብ ጭፍጨፋ እንዲቀጥል እየተባበረ ያለ ኤሊት ነው ብየ በድፍረት እናገራለሁ” ቀጥሎም “ የአማራ ልሂቅ አሁን ያለው የጎሳ ስርዓት ስር እንዲቆም እና እግሩን እንዲዘረጋ ከፍተኛ አስተዋፆ አድርጓል” ይላል። ኢትዮጵያ ዉስጥ የጎሳ ስርዓትን የተከለው የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ግንባር (ህወሃት) እንደሆነ ልብ ይሏል። ቴወድሮስ የአማራ ልሂቅን የሚከሰው የብአዴንን ወንጀል ሁሉ ሰብስቦ ለአማራ ልሂቅ በማሸከም ነው። እዉነታው ግን ከወያኔ ጋር ሁነው የዘር ፖለቲካን የተከሉት እነ በረከት ስምዖን፣ አዲሱ ለገሰ እና ታደሰ ካሳ አይነት የብአዴን ጉምቱወች አማራ አይደሉም፣ ወያኔ የዘር ፖለቲካን ለመትከል በአማራ ላይ የጫናቸው የህወሃት ወኪሎች ነበሩ።
 

 
አብዛኛው የአማራ ልሂቅ ህወሃት ጠፍጥፎ ከሰራው ብአዴን ተቃራኒ ቁሞ የህወሃትን የዘር ፖለቲካ ሲቃወም እና ሲታገል እንደኖረ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርብ የሚከታተል ሁሉ የሚያውቀው ሃቅ ነው። የአማራ ብሄርተኝነትም ወያኔ በተከለው የዘር ፖለቲካ እና መንግስታዊ ስርዓት እየተፈጠረው ያለ ያለፉት 3 ዓመት ክስተት ነው። ቴወድሮስ ብአዴንን ወይም ሌላ ድርጅት በስም ጠርቶ ተጠያቂ ቢያደርግ ችግር አልነበረውም። “ለባርነት ተሽቀዳድሞ ያልተመረጠው የአማራ ልሂቅ” በተሰኘው ፕሮግራሙ ላይ ህወሃት እና ኦነግን በስማቸው ጠራ እንጅ የትግራይ እና የኦሮሞ ልሂቃን ብሎ በደፈናው ተጠያቂ አላደረገም፣ አንድም ቦታ የትግራይ ልሂቅ ሲል አትሰሙትም፤ የአማራ ሲሆን ግን "የአማራ ልሂቃን" እያለ አደገኛ በሆነ መልኩ በጅምላ ይፈርጃል። እዉነት እንነጋገር ከተባለ የአማራ ልሂቅ በፖለቲካ አመለካከቱ እና አቋሙ ቢመዘን እንኳን ብዙ አይነት ነው፣ እንዲያውም ከአማራ ልሂቅ በበለጠ የትግራይ ልሂቅ አብዛኛው የህወሃት ካምፕ ውስጥ ነው የሚገኘው፤ ቢሆንም የትግራይ ልሂቅ ተብሎ በደፈናው የህወሃት ወንጀል ተሸካሚ ሊሆን አይገባም፣ ምክንያቱም አንደኛ አንድም ሰው ቢሆን ያለወንጀሉ በሌሎች ወንጀል ተጠያቂ መሆን ስለሌለበት፣ ሁለተኛ ልሂቅ የሚል ጅምላ ፍረጃ ተጠቅሞ ተጠያቂ ማድረግ ሁሉንም የማህበረሰብ አባላት ለአደጋ ስለሚያጋልጥ ነው፣ በእንግሊዝኛ 'ስሊፐሪ ስሎፕ' እንደሚባለው ነው። ቴወድሮስ ይሄ ጠፍቶት ነው የሚል ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ የለኝም፣ ምን እንደሚሰራ በደንብ ያውቃል። 
 
ቴወድሮስ የአማራ ልሂቃን ብሎ በድፍረት በጅምላ የሚከሰዉን ያህል፣ የትግራይ ልሂቃን ብሎ አንድም ቀን ከሶ አያውቅም፣ ማስረጃ የሚፈልግ ካለ የዩቱብ ቻናሎቹ ላይ ያሉትን በመቶወች የሚቆጠሩ ፕሮግራሞች ይፈትሽ። በተጨማሪም የአማራ ልሂቃን ላይ በግል እያራከሰ ተከታታይ ፕሮግራሞችን ሲሰራ፣ በአንድም የትግራይ ልሂቅ ላይ በግል የሚያራክስ ፕሮግራም ሰርቶ አያውቅም። በቴወድሮስ ራሱን የቻለ የማራከስ ፕሮግራም ከተሰራባቸው ግለሰቦች መካከል ዲያቆን ዳንኤል ክብረት (4 ተከታታይ ፕሮግራሞች)፣ ታማኝ በየነ፣ ቴዲ አፍሮ እና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል። በተቃራኒው ሃገርን በዘር ሸንሽነው፣ የዘር ፖለቲካ እና ህገመንግስት ተክለው፣ ህዝብ ጨፍጭፈው መቀመቅ የከተቱት የህወሃት ባለስልጣናት (ስብሃት ነጋ፣ ቴወድሮስ አድሃኖም፣ ጌታቸው ረዳ፣ ደብረፅዮን ወዘተ) ላይ ቴወድሮስ ፀጋየ በግል አንድም ፕሮግራም ሰርቶ አያውቅም። ከዚህ ላይ ግለሰቦች አይተቹ አልልም፣ ካጠፉ መነቀፍ አለባቸው፤ ነገርግን ዘር እየተመረጠ ከሆነ ፕሮግራም የሚሰራባቸው፣ ትችቱ በጥፋታቸው ሳይሆን በዘራቸው ነው ወደሚል መደምደሚያ ያደርሰናል፤ የአማራ ልሂቃንን እንበቀላለን የሚለው አደገኛ ትርክት ሰለባ እንደሆኑ አስረጅ ይሆናል። 
 
"የአማራን ልሂቃን" እያሉ በጅምላ ተጠያቂ የማድረግ እና ለጭፍጨፋ የማዘጋጀት ትርክት ህወሃት ሆን ብሎ የቀመረው እና እየረጨው ያለው መርዝ ነው። ሰሞኑን የህወሃት አፈቀላጤ ጌታቸው ረዳ በሰጠው ቃለምልልስ “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ትልቁን አስተዋፆ የአማራ ኢሊት ነው የሚወስደው… ከአማራ ኢሊት ጋር ሂሳብ እናወራርዳለን” ይላል። [https://www.facebook.com/Mastewal.D/posts/10160058666659897] ምን ማለቱ ነው? ወያኔ እንደትናንቱ ቀንቶት ጥርስ ካበቀለ የአማራ አስኳል የሆነውን ሁሉ ፈጅተን አማራን በጨለማ የሚኖር ህዝብ እናደርገዋለን፣ እንጨፈጭፈዋልን፤ 30 ዓመት ሙሉ ነፍጠኛ እና ትምክህተኛ የሚል ስም ለጥፈን እንዳሳደድነው እና እንደገደልነው፣ አሁን ደግሞ የአማራ ልሂቅ የሚል ሌላ ለትርጉም ክፍት የሆነ ቃል ተጠቅመን እንደ አመችነቱ እየተረጎምን ህፃናትን፣ ሴቶችን እና ንፁሃንን እንጨፈጭፋለን እያለ ነው። 
 
አገርን በዘር የከፋፈሉት፣ በኋላም በዕብሪት ተወጥረው በለኮሱት ጦርነት ሃገር ያፈረሱት እራሳቸው ወያኔወች ሁነው እያለ፣ የአማራ ልሂቅን ሃገርን በማፍረስ የሃሰት ክስ በጅምላ ወንጀለኛ አድርገው የሚፈርጁት፣ ከቀናቸው ለነገ ጅምላ ጭፍጨፋ ለማዘጋጀት እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል። ወያኔ ከ47 ዓመት በፊት የአማራን ገዥ መደብ ነው የምታገለው ብሎ በማኒፌስቶው ፅፎ ላለፉት 30 ዓመታት አማራን አሳደደ፣ ገደለ፣ መንግስታዊ መዋቅር ዘርግቶ ግድያዉን እና ማሳደዱን አስፈፀመ፤ ዛሬ ደግሞ ትርክቱን አስፍቶ “የአማራ ልሂቅን” እበቀላለሁ ይላል። “የአማራ ልሂቅ” በሚል ሽፋን ህዝቡን ጭራቅ አስመስሎ የመሳል ትርክቱ መሬት ሲቆነጥጥ፣ ዛሬ በማህፀን ያለ ፅንስ ነፍጠኛ ተብሎ ከሆድ በሳንጃ እንደሚወጣው ሁሉ፣ ነገ ደግሞ “የአማራ ልሂቅ” የሚል ተጨማሪ ፍረጃ ተመርቆለት ሆድ እየተቀደደ ይገደላል። 
 
ከላይ ባቀረብኩት ፅሁፍ ላይ ከዘለፋ እና ስድብ ርቆ በጭዋነት ሊከራከረኝ የሚፈልግ ሰው ካለ በገለልተኛ ሚዲያ እና አወያይ ፊት ለፊት ቀርቤ ለመከራከር ዝግጁ መሆኔን እገልፃለሁ።
 

 

0/Post a Comment/Comments