የፋሽሽቱ የትግራይ ወራሪ ቡድን በአማራ ህዝብ ላይ በወራራ ያደረሰው የንብረት ውድመት ከ340 ቢሊዮን ብር በላይ ነው!!

የአማራ ክልል በግብርና ዘርፍ ላይ ከ340 ቢሊዮን ብር በላይ ውድመት እንደደረሰበት አስታወቀ
6 February 2022
አማኑኤል ይልቃል


የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ጦርነት በተደረገባቸው ዘጠኝ ዞኖች ላይ ሦስት ወራት የፈጀ ጥናት አድርጎ፣ በግብር ዘርፉ ላይ የ340.6 ቢሊዮን ብር ውድመት እንደደረሰ ማረጋገጡን አስታወቀ፡፡

አማራ ክልል ውስጥ ካሉት 11 ዞኖች ውስጥ በዘጠኙ ጦርነት የተካሄደ መሆኑን፣ በእነዚህ ዞኖች ውስጥ የሚገኙ 76 ወረዳዎች ላይ በግብርናው ዘርፍ ጉዳት መድረሱ በጥናቱ ላይ ተመላክቷል፡፡ ጦርነት በተደረገባቸው እነዚህ ዞኖች ውስጥም 9.8 ሚሊዮን ሕዝብ እንዳለ ታውቋል፡፡  

ሪፖርተር የተመለከተው የክልሉ የጥናት ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ ጦርነት ከተደረገባቸው ዘጠኝ ዞኖች ውስጥ በሰሜን ወሎና ዋግ ህምራ ዞኖች ላይ የደረሰው ጉዳት መጠን ደረጃ ‹‹እጅግ በጣም ከፍተኛ›› ነው፡፡ ከዚህ በላይ እነዚህ ዞኖች አሁንም በጦርነት ቀጣና ውስጥ እንደሆኑ በጥናት ሪፖርቱ ላይ ተቀምጧል፡፡ ሌሎች አራት ዞኖች የደረሰባቸው ጉዳት ‹‹በጣም ከፍተኛ›› በሚል የተቀመጠ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ሦስት ዞኖች የደረሰባቸው ጉዳት ‹‹ከፍተኛ›› የሚል ደረጃ ተሰጥቶታል፡፡

ጥናቱ በመጀመርያ ሁለት ወራት ፈጅቶ እስከ መስከረም 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ እንደተደረገ ለሪፖርተር የተናገሩት የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አልማዝ ጊዜው (ዶ/ር)፣ ከመጀመርያው ጥናት በኋላ ጦርነቱ እስከ ሰሜን ሸዋ ድረስ በመምጣቱ አካባቢዎቹ በድጋሚ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ አንድ ወር የፈጀ ተጨማሪ ጥናት ተደርጓል፡፡

አልማዝ (ዶ/ር) በክልሉ ካሉ የተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ አሥር ከፍተኛ ባለሙያዎችን የያዘ ቡድን፣ ጉዳት በደረሰባቸው ቦታዎች ላይ በመገኘት ጥናቱን እንዳከናወነ አስረድተው፣ ሙሉው ጥናት ተጠናቅሮ የተጠናቀቀው ጥር 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ነው ብለዋል፡፡

ለመጀመርያ ጊዜ በተደረገው ጥናት የተገኘው የጉዳት መጠን 266 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገው ጥናት 74 ቢሊዮን ብር በመጨመር ጠቅላላ ጉዳቱን ወደ 340 ቢሊዮን ብር አሳድጎታል፡፡ ጥናቱ በክልሉ ያሉ የግብርና ምርቶች፣ የግብርና ቢሮዎች፣ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቶች፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲዎች፣ እንዲሁም የእንስሳት ሀብት ልማት ኤጀንሲዎች የዳሰሰ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የተገኘው አጠቃላይ የጉዳት መጠን በገንዘብ 340,626,890,796 ብር ነው፡፡

ጥናቱ ያመላከተው የአማራ ክልል ግብርና ዘርፍ ጉዳት የ2014 ዓ.ም የፌዴራል በጀት የሆነው 561.7 ቢሊዮን ብር 60 በመቶ ነው፡፡ ክልሉ ለተያዘው በጀት ዓመት ያፀደቀው 80.1 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ አሁን በክልሉ የግብርና ዘርፍ ላይ ደርሷል የተባለው ጉዳት ከአማራ ክልል የ2014 ዓ.ም በጀት ከአራት እጥፍ በላይ ይልቃል ተብሏል፡፡

በጥናት ሪፖርቱ ላይ የግብርና ቢሮ የሚለውና እንደ የሰብል ምርት ግምት፣ መስኖ መሠረተ ልማት፣ ዞኖችና ወረዳዎች የቢሮ ግንባታ፣ መሠረተ ልማት፣ ተሽከርካሪና ቁሳቁሶች የሚሉትን የያዘው የግብርና ዘርፍ ከሌሎቹ የግብርና ዘርፎች የበለጠ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ዘርፉ 218.5 ቢሊዮን ብር ጉዳት የደረሰበት መሆኑን፣ ከዚህ ውስጥ 123.6 ቢሊዮን ብር የተገመተው ውድመት የደረሰው በሰብል ምርት ላይ ነው ተብሏል፡፡ በሰብል ምርት ላይ የደረሰው ይህ ጉዳት በክልል ተቋሙ ውስጥ በመቶኛ ያለው ድርሻ 56.6 በመቶ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡



በጥናቱ ላይ የእንስሳት ሀብት ልማት ኤጀንሲ በሚለው ዘርፍ ሥር የደረሰው ውድመት በሁለተኝነት የተቀመጠ ሲሆን፣ ይህ ዘርፍ የ94.3 ቢሊዮን ብር ውድመት ደርሶበታል ተብሏል፡፡ በዚህ ውስጥም በእንስሳት ዕርባታ ግብዓት ላይ 52.6 ቢሊዮን ብር እንዲሁም በአርሶ አደሮች እንስሳት ላይ የ31.4 ቢሊዮን ብር ጉዳት መድረሱ ተመልክቷል፡፡

በጥናቱ መሠረት በመሠረታዊ ማኅበራት የቢሮ ግንባታና ቁሳቁሶች ላይ የደረሰው ጉዳት 20.6 ቢሊዮን መሆኑን፣ ይህም በክልሉ ውስጥ ያለው ድርሻ 85.8 በመቶ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በምርምር መሠረተ ልማት፣ በተሽከርካሪና በቁሳቁሶች ላይ የደረሰው የ2.4 ቢሊዮን ብር ጉዳት ደግሞ በክልሉ የግብርና ዘርፍ ላይ ያለው ድርሻ 89 በመቶ መሆኑ ታውቋል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አልማዝ (ዶ/ር) እንደተናገሩት አሁን የደረሰው ጉዳት ለአሥርት ዓመታት ሲገነባ የቆየውን ዘርፍ በከፍተኛ መጠን የጎዳ ነው፡፡ ይህም ጉዳት በክልሉ 31 በመቶ የሆኑትን ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ እንዲሁም የምግብ ዋስትና ያላረጋገጡ ሰዎች ቁጥር እንዲጨምር ያደርጋል ብለዋል፡፡

ጉዳቱ የደረሰው በክልሉ ባሉ 76 ወረዳዎች ላይ እንደሆነ የጠቀሱት አልማዝ (ዶ/ር)፣ በ76 ወረዳዎች የሚገኙ የግብርና ጽሕፈት ቤቶች ባዶ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አክለውም ‹‹ለምሳሌ የኦሮሞ ብሔረሰብ ግብርና ዘርፍ ከዚህ ቀደም 80 መኪኖች ነበሩት፡፡ አሁን ሁሉም የሉም፣ አንድ መኪና ብቻ ነው የሰጠነው፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ እንደ ደሴ ቲሹ ካልቸር፣ እንዲሁም የስንሪቃና የአበርገሌ ግብርና ምርምር ማዕከላት ላይ የደረሰው ውድመት በቀላሉ የሚተካ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ ስሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከልና ደሴ ቲሹ ካልቸርን መደበኛ ሥራ ለማስጀመር ሕንፃቸው ፈርሶ በድጋሚ መሠራት እንዳለበት አልማዝ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ የግብርና ቢሮው የሲሪንቃ ምርምር ማዕከል በቆርቆሮ ተሠርቶ ሥራ እንዲጀምር ማድረጉንም አክለዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ በሰብል ምርት 33 በመቶ፣ በእንስሳት ደግሞ 28 በመቶ ድርሻ ባለው የአማራ ክልል የግብርና ዘርፍ ላይ የደረሰው ጉዳት ከክልሉ ያለፈ አገራዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡ ውድመቱ ካለው አገር አቀፋዊ ተፅዕኖ የተነሳም አገሪቱ የዘላቂ የልማት ግቦችንም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ መሪ ዕቅድ ተብለው የተቀመጡትን ግቦች ለማሳካት አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሚኖር ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ በዘርፉ ላይ የደረሰውን ጉዳት መልሶ ለመገንባት የሚያስችል ዕቅድ እንዳዘጋጀ የገለጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ፣ ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ ከክልሉ መንግሥት፣ እንዲሁም ከፌዴራል ምን ያህል ሀብት መገኘት እንዳለበት እንደሚዘረዝር አብራርተዋል፡፡

አልማዝ (ዶ/ር) በግብርና ዘርፉ ላይ የደረሰው ጉዳት የምግብ እጥረት ሊፈጥር ይችላል የሚል ሥጋት እንዳለ ገልጸው፣ ይህ እንዳይከሰት በመጪው በልግ ወቅት ምርት ለማምረት እንዲቻል እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም ሲባል ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የግብርና ሥራ ለመሥራት የሚያስችል ዘር፣ ማዳበሪያ፣ የመስኖ መሣሪያና ሌሎች ግብዓቶችን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥያቄ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡

ጉዳት የደረሰባቸው የግብርና ምርምር ማዕከላትም ወደ መደበኛ ሥራቸው እስኪመለሱ ድረስ፣ በግብርና ምርት ላይ እንዲሰማሩ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር ከፍተኛ ተመራማሪ አረጋ ሹመቴ (ዶ/ር)፣ በግብርና ዘርፉ ላይ ደረሰ የተባለው ጉዳት በገንዘብ መተመን የቻለው ጉዳት ብቻ እንደሆነ ጠቅሰው በዚህ ምክንያት የሚደርሰው ማኅበራዊና የጤና ቀውስ ከፍተኛ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በጥናቱ ላይ የተጠቀሰው ቁጥር አሁን የደረሰውን ጉዳት ብቻ እንጂ፣ አሁን በደረሰው ውድመት ምክንያት በቀጣዮቹ ዓመታት ሳይመረት የሚቀረውን ምርት እንደማያካትት ገልጸዋል፡፡

ተመራማሪው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ተመሳሳይ ሁኔታው ውስጥ ያለፉ አገሮችን ተሞክሮ በጦርነቱ የተጎዱ ክልሎች ላይ መተግበር እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ የፌዴራሉ መንግሥት የመልሶ ግንባታ መሪ ዕቅድ አውጥቶ እነዚህን ክልሎች በተለየ ሁኔታ ማየት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ክልሎቹም በጦርነቱ ያልተጎዱባቸው አካባቢዎች ላይ የሚገኙ ሀብቶችን ማዘዋወር፣ ያልተጎዱ የክልሉ ዞኖች የሌሎቹን አካባቢዎች ምርት በሚያካክስ መንገድ  እንዲያመርቱ ማድረግ አንድ አማራጭ መሆኑን አረጋ (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡

ይሁንና እንደ ባለሙያው አስተያየት የመልሶ ግንባታ ሥራው ውስጥ ከመገባቱ በፊት፣ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ጦርነቱ የሚቋጭበትና ጉዳቱ ተመልሶ የማይከሰትበትን መንገድ መፈለግ አለባቸው፡፡

ጥር 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ሦስተኛ ልዩ ስብሰባውን ያካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ማፅደቁ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ተጨማሪ በጀት ውስጥ 90 ቢሊዮን ብር ለመከላከያ ሠራዊት ስንቅና ትጥቅ የሚውል ሲሆን፣ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት አምስት ቢሊዮን ብር ተበጅቷል፡፡

 ምንጭ: https://ethiopianreporter.com/index.php/article/24592


*************


 












 

 

******









*********



















 

0/Post a Comment/Comments